2014 ሜይ 19, ሰኞ

ግንቦት 11 ቅዱስ ያሬድ ካህን


  
            በ ዲ.ዮርዳኖስ አበበ
"+ እንኩዋን ለታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ዓመታዊ የዕረፍት (የመሰወር) በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

=>ቅዱስ ያሬድ:- ከእግዚአብሔር ያገኘነው አባታችን: ክብራችን: ሞገሳችን ነውና በምን እንመስለዋለን? አንደበቱ ጣፋጭ (ጥዑም): ልቡናው የቅድስና ማሕደር: ሕሊናው የምሥጢራት ሠረገላ ነው:: እስከ አርያም ተነጥቆ የማይፈጸም ምሥጢርን የተመገበ ማን እንደርሱ!

+ሊቀ ሊቃውንት እዝራ ሐዲስ እንደሚሉት:- "ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከራስ ጸጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ: ሙሉ አካሏ ነው"



=>የሊቁ ዜና ሕይወት በጥቂቱ:-
+ቅዱስ ያሬድ የተወለደው በ505 ዓ/ም አክሱም አካባቢ ሲሆን እናቱ ክርስቲና (ታኡክልያ) አባቱ ደግሞ ይስሐቅ (አብድዩ) ይባላሉ:: ሊቁ በሕጻንነቱ ምሥጢር (ትምሕርት) አልገባው ብሎ ይቸገር ነበር:: ትምሕርት እንቢ ያለው ሰነፍ ስለ ነበር አይደለም:: በጥበበ እግዚአብሔር እንጂ::

-ምን ትምሕርት ባይገባው ጾምና ጸሎትን ያዘወትር ነበር:: ልቡናው ደግሞ በእመቤታችንና በልጇ ፍቅር የታሠረ ነበር:: አንድ ቀን ግን መምሕሩ የነገሩት ቀለም አልያዝሕ አለው:: ሲፈትኑትም ባለመመለሱ ተገረፈ:: ዱላው በጣም ስለተሰማው ቅዱሱ ከመምሕሩ ኮብልሎ ማይ ኪራሕ አካባቢ ሲደርስ ደክሞት አርፎ እግዚአብሔር ትጋትንና ተስፋ አለመቁረጥን ከትል አስተማረው:: ትሏ 6 ጊዜ ወድቃ በ7ኛው ፍሬዋን ስትበላት ተመልክቷልና:: ከዚህ በሁዋላ ቅዱስ ያሬድ ወደ መምሕሩ ተመልሶ: ይቅርታ ጠይቆ ትምሕርት ጀመረ::

-ሊቁም ትጋትንና ጸሎትን ከሰጊድ ጋር አበዛ:: እግዚአብሔር ደግሞ በድንግል እናቱ አማካኝነት የምሥጢር ጽዋን አጠጣው:: ካህኑ ያሬድ እንዲያ አልገባህ ያለው ምስጢር ተገልጦለት በጥቂት ጊዜ ብሉይ ከሐዲስ ወሰነ::በምሥጢር ባሕርም ይዋኝ ጀመር::

-ያን ጊዜ ሰማያዊ ዜማ አልተገለጠም ነበርና በጸሎት ላይ ሳለ ተደሞ መጣበት:: 3 መላእክት በወፎች አምሳል መጥተው አነጋገሩት:: ድንገትም ነጥቀው ወደ ሰማያት: ወደ ልዑላኑ መላእክት ዘንድ አደረሱት:: ሊቁ በሰማያት ልዩ ምሥጢር: ልዩ ምስጋናና ልዩ ዜማን አዳመጠ:: ይሕንን ምስጋና ብዙ ቅዱሳን ቢሰሙትም ቅዱስ ያሬድ ግን ይዞት እንዲወርድ ተፈቀደለት::

-ሊቁ ወደ ምድር ተመልሶ በታላቅ ተመስጦ አክሱም ጽዮን ውስጥ በሃሌታ አመሰገነ:: ሕዝቡና ንጉሡም ከጣዕሙ የተነሳ አደነቁ:: ቅዱስ ያሬድ ለተወሰነ ጊዜ በአክሱምና ደብረ ዳሞ ሲያገለግል ቆይቶ: ከመሬት ክንድ ከስንዝር ከፍ ብሎ ለእመቤታችን አንቀጸ ብርሃንን ደርሶላት ከሃገሩ ወጣ::

-ቅዱስ ያሬድ በቀሪ የሕይወቱ ዘመናት:-
1."5" ያሕል መጻሕፍትን ጽፏል
2.በጣና ቂርቆስ: በዙር አባና በሌሎችም ቦታዎች ወንበር ዘርግቶ ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርቷል
3.በሰሜን ተራሮች አካባቢ በትጋሃ መላእክትና በተባሕትዎ ኑሯል
-በ576 ዓ/ም በተወለደ በ71 ዓመቱ በዚህች ቀን ተሰውሯል::

-አባቶቻችን:-
-ጥዑመ ልሳን
-ንሕብ
-ሊቀ ሊቃውንት
-የሱራፌል አምሳያ
-የቤተ ክርስቲያን እንዚራ
-ካህነ ስብሐት
-መዘምር ዘበድርሳን
-ማኅሌታይ
-ልዑለ ስብከት
እያሉ ይጠሩታል::

=>የቅዱሱ ጸሎትና በረከት ሃገራችንን ከክፉው ሁሉ ይጠብቅልን::

=>ግንቦት 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ያሬድ ካህን ወማኅሌታይ
2.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ
3.ክርስቲናና ይስሐቅ (የቅዱስ ያሬድ ወላጆች)
4.ቅድስት ታውክልያ እናታችን (ንግሥናን ንቃ ሰማዕት የሆነች)
5.ቅድስት ኤፎምያ ሰማዕት
6.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
7.ቅድስት አናሲማ ገዳማዊት
8.አባ በፍኑትዮስ ገዳማዊ
9.አባ አሴር ሰማዕት (ኢትዮዽያዊ)
10.አባ በኪሞስ ጻድቅ


=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት
2.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
3.ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና

=>+"+ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ:: እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ:: በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደሆነ አላውቅም:: እግዚአብሔር ያውቃል:: ወደ ገነት ተነጠቀ:: ሰውም ሊናገር የማይገባውን: የማይነገረውን ቃል ሰማ:: +"+ (2ቆሮ. 12:2-5)

<ወስብሐት ለእግዚአብሔር>

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...